value="
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ በመሬትና መሬት ነክ ጉዳዮች ዙሪያ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ጋራ ሰኔ 13/2016ዓ.ም የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርመዋል፡፡
የመግባቢያ ሰነዱን የተፈራረሙት የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ጌታቸው ሰነዱን በተፈራረሙት ወቅት እንደገለፁት ቢሮው በዘርፉ የሚስተዋለውን ብልሹ አሰራሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ ባለፉት ስድስት ወራት በጥናት ላይ የተመሰረት ተቋማዊ ሪፎርም በማድረግ የብልሹ አሰራር ዋነኛ መንስኤ የነበሩ ከ726‚150ሺ ፋይሎችን ስካን በማድረግ ለኦንላይን አገልግሎት ዝግጁ መደረጉን ገልፀው ይህም ህገወጥ ሰነዶችን በቀላሉ የሚለይ በመሆኑ ፋይዳው ለሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ አገልግሎት ጭምር የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ቢሮው በአዲስ አስተሳሰብ ራሱን አደራጅቶ በግብዓትና በሰው ሃይል አጠናክሮ በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመታገዝ በስሩ ካሉት ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ጋር የቴክኖሎጂ ትስስር በመፍጠር የሰነድ መጥፋት፣የባለጉዳይ መጉላላትና ብልሹ አሰራርን የሚያስወግድ አሰራር መሆኑን አብራርተዋል።
ቢሮ ኃላፊ በበኩላቸው አሁን ካለው አገሪቱ የእድገት ሁኔታና የዜጎች ፈጣን የመንግስት አገልግሎት የማግኘት ፍላጎት በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ለዜጎች ማቅረብ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተናግረዋል ።የቢሮ ሃላፊው አክለውም ሌሎችም ተቋማት ወደ እዚህ ቴክኖሎጂ ትስስር እንዲመጡ በማድረግ ላይ የሚገኝ መሆኑን ጠቅሰው ይህንን የቴክኖሎጂ ትስስር ይበልጥ ለማዳበርና ለውጥ ለማምጣጥ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የሰነዶች ማረጋገጫ ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀሚድ ኪኒሶ በበኩላቸው በየጊዜው ከሰነዶች ጋር የተያያዘ ከፍተኛ የማጭበርበር ወንጀል እየተፈፀመ መሆኑን አውስተው በቴክኖሎጂ የታገዘ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋት በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ተቋሙ ተገልጋዮች ወደ ተቋሙ ሳይመጡ አስቀድመው ለአገልግሎቱ ሰዓት የሚይዙበት ሁኔታ ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ቢሮው ለሚሰጠው ቀልጣፋ አገልግሎት የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ መሬትና መሬት ነክ ጉዳዮችን በቴክኖሎጂ ትስስር የያዘውን መረጃ እንድንጠቀምበት ላደረገው የቴክኒክ ድጋፍና እገዛ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡፡ በሁለቱ ተቋማት የሰነድ አደረጃጀቱና አገልግሎቱ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን በማድረግ እና ከሌሎች ተቋማት ጋር የመረጃ ትስስር እንዲኖር ላደረጉ የስራ ሃላፊዎችንና ባለሙያዎችን አመስግነዋል።
በመጨረሻም የመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ተዘዋውረው በመጎብኘት ተቋሙ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ያደረገውን ስርነቀል ለውጥ አድናቆታቸውን ገልፀዋል፡
በሁለትዮሽ የመግባቢያ ስነድ የፊርማ ስነስርዓት ላይ የመሬት ልማት አስተዳደር ቢሮ እና ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት አመራሮች እና የስራ ኃላፊዎች በፊርማ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።
"