ህትመቶች

የዜጎች ቻርተር 2016

image description

1.መግቢያ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማዋን ሁለንተናዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በማስገባት ዜጎቿ የዚህ ለውጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ዘርፈ-ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል። ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል የአገልግሎት አሰጣጡን ተደራሽ እና የህብረተሰቡን ፍላጎት ያማከለ እንዲሆን ለማድረግ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የለውጥ መሳሪያዎችን ተግባራዊ ሲያደርግ ቆይቷል። በዚህ ሂደት በርካታ ለውጦች የታዩ ቢሆንም አሁንም ድረስ የህብረተሰቡን ፍላጎት በተገቢው ማሟላት እና የተገልጋዩን እርካታ በሚፈለገው ልከ ማድረስ አልተቻለም ።
አሁን በየደረጃው ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚታየውን ችግር በመፍታት የተገልጋዩን ፍላጎት ለማሟላት እና ብሎም የነዋሪዎቿን እርካታ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሚያስችል ለውጥ ማምጣት ያስፈልጋል። ነዋሪው ፈጣን፣ ተደራሽ እና ጥራት ያለው አገልግሎት በዝቅተኛ ዋጋ ማግኘትን ይፈልጋል። ይህንን ዕውን ከማድረግ አንፃር ደግሞ የአገልግሎት አሰጣጡን ቀልጣፋ፣ ተደራሽና ዘመናዊ ማድረግ እንዲሁም ቀጣይነት ባለው መልኩ እያደገና እየተሻሻለ የሚሄድ ሊሆን ይገባል።
ለአገልግሎት አሰጣጥ ማነቆዎቹ በመንስኤነት ከሚጠቀሱ ምክንያቶች አንዱ የለውጥ የሪፎርም ፕሮግራምን በተግባር ወደ መሬት ለማውረድና ለማስፈጸም በተለያዩ ጊዜያት በስራ ላይ የዋሉት የለውጥ መሣሪያዎች አንዱ ሌላውን በሚተካበት ወይም እያንዳንዱ በተናጥል የሚተገበሩ ቴክኒካዊ ስራዎች ሳይሆኑ በተመጋጋቢነት ተሳስረው የሚተገበሩ ፖለቲካዊ ሥርዓቱ ትኩረት ያደረገባቸውን የልማትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ግቦች ማሳኪያ መሳሪያዎች መሆናቸውን ተገንዝቦ በባለቤትነትና በቁርጠኝነት ይዞ አቀናጅቶና አስተሳስሮ ያለመምራት ክፍተት ነው፡፡
ከላይ የተጠቀሱትንና ሌሎችንም በመንግስት መ/ቤቶች የሚታዩትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮች ከመፍታት አኳያ አቅም ሊፈጥር የሚችልና በሌሎች አገሮች ተግባራዊ ተደርጎ ውጤታማ የሆነውን የዜጎች ቻርተር አሰራር ከሌሎች የለውጥ መሣሪያዎች ጋር አስተሳስሮ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ቢሆንም በሚፈለገው ደረጃ እየተተገበረ ነው ማለት አይቻልም፡፡
በመሆኑም የተቋማትን አፈጻጸም ትርጉም ባለው መልኩ ለመለወጥ፣ ከዜጎች ለሚነሱ የመልካም አስተዳደር ዕጦት ጥያቄዎች ፈጣን፣ ውጤታማና ቀልጣፋ ምላሽ ለመስጠት እንዲሁም የተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ ፍትሃዊነትና የህግ የበላይነትን መርሆዎች ተከትሎ የተደራጀና የተቀናጀ የልማት ተሳትፎ የተጀመረውን የልማትና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አጀንዳ ግለቱን ጠብቆ ለማስቀጠል አጋዥ የለውጥ መሳሪያ እንዲሆን ታስቦ የተቀረጸውን የዜጎች ቻርተር አሰራር አጠናክሮ መተግበር አስፈልጓል፡፡
ስለሆነም በመሬት ልማትና አስተዳደር ቢሮ ይህን የዜጎች ቻርተር እና የትግበራ ማንዋል በማዘጋጀት በቢሮ እና በስሩ የሚገኙ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ሊከተሏቸው የሚገቡ አካሄዶችን በማመላከት የቻርተሩን አስፈላጊነትን፣ የአዘገጃጀት ደረጃዎችን፣ የአተገባበር ሂደቶችን፣ የክትትል፣ግምገማና ክለሳ ስርዓትን አካቶ የያዘ ማንዋል ተዘጋጅቷል፡፡