የመሬት ይዞታና አስተዳደር በ2002ዓ.ም መመሪያ ቁጥር 2/2002ዓ.ም የወጣ መመሪያ
በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የመሬት ይዞታና አስተዳደር በተሻለና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲሁም ውስን የሆነውን የመሬት ሀብት አጠቃቀም በተገቢው ሁኔታ ለማስተዳደር፤ ህገወጥነትን ለመከላከል እንዲያስችል የከተማው አስተዳደር ልዩ ትኩረት ሰጥቶበት በ2002ዓ.ም መመሪያ ቁጥር 2/2002ዓ.ም ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት መመሪያው ከወጣበት ቀን ጀምሮ የመሬት ይዞታ አገልግሎቶችን በመመሪያዉ መሰረት ሲሰጥ ከመቆየቱም በላይ የተሟላ የይዞታ ባለመብትነት ሰነድ የሌላቸዉን ባለይዞታዎችን የሬጉላራይዜሽን መስተንግዶ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እያለ አዲስ የሊዝ አዋጅ በመውጣቱና የመዋቅር ለውጥ በመደረጉ እንዲሁም በነባሩ መመርያ ላይ በትግበራ ወቅት አንዳንድ ክፍተቶች በመታየታቸው እና በመመሪያው ያልተዳሰሱ ጉዳዮች በመገኘታቸው መመርያውን እንደአዲስ ማስተካካልና ማውጣት አስፈላጊ ሆኗል፡፡ የከተማ ቦታ በህግ ለሚፈቀድላቸዉ ሰዎች እና ሰነድ ያላቸው ህጋዊ ባለይዞታዎች የሚጠይቁአቸውን የተለያዩ መስተንግዶዎች ከሊዝ አዋጁና አዋጁን ለማስፈጸም ከወጣው ደንብ ጋር በተጣጣመ መልኩ ምላሽ ለመስጠት እንዲቻል መመሪያውን ለማሻሻል በማሰብ የከተማው አስተዳደር በተሰጠው ስልጣንና ኃላፊነት መሰረት ይህ መመሪያ ለከተማው አስተዳደር ካቢኔ ቀርቦ ይህ የይዞታ አስተዳደር መመሪያ ቁጥር 12/2004 ዓ.ም ወጥቷል፡፡